ድብረት ምንድን ነው

ድብረት ምንድን ነው

ድብርት በአንድ ሰው አስተሳሰብ ፣ ስሜት እና በተግባር ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድር ሀዘን ፣ ገለልተኛነት እና ተስፋ የመቁረጥ ስሜት ተለይቶ የሚታወቅ የአእምሮ ህመም ነዉ። ድብርት ደስታን በሚያመጡ ነገሮች ላይ ከፍተኛ ፍላጎት ማጣትን ያመጣል። የአንድን ሰው ሀሳቦች ፣ ባህሪ ፣ ተነሳሽነት ፣ ስሜቶች እና ደህንነትንም ይለውጣል፡፡ ድብርት ያጋጠማቸው ሰዎች የመጥፎ ስሜት ፣ የተስፋ መቁረጥ ስሜት ይኖራቸዋል እናም በአንድ ሰው የዕለት ተዕለት ሕይወት ውስጥ ከፍተኛ ተጽዕኖ ያሳድራል፣ ከፍ ሲልም ራስን የማጥፋት ሀሳቦችን ሊኖሯቸው ይችላል።

ድብርት በተለያዩ ምክኒያቶች ሊከሰት ይችላል ለምሳሌ

• ሐዘን-የሚወዱትን ሰው በ ሞት ማጣት

• የገንዘብ ጫና- የገንዘብ ማጣት የሚፈጥረው ጭንቀት (በተለይ አሁን ላይ እንደበፊቱ ሥራ ሥለማይሰራ)

አስጨናቂ የሕይወት ክስተቶች – ( አካላዊ ፣ ወሲባዊ ወይም ስሜታዊ በደሎች )

• የተወሰኑ የህክምና መድኃኒቶች – (ለካንሰር፣ለልብ፣Parkinson፣ seizure ህመሞች የሚወሰዱ መድሀኒቶች)

• ስነ-ባህሪ ( genetics ) – እናት ወይም አባት ድብርት ካለባቸው ልጃቸው የመያዝ እድሉ ይጨምራል

• አካባቢያዊ – አስጨናቂ የልጅነት ገጠመኞች

• ባህላዊ እምነቶች – ወንዶች ማልቀስ የለባቸውም አይነት ማህበራዊ ጫናዎች

• ጉርምስና – የጉርምስና ዕድሜ በስሜትና በባህሪ ከፍተኛ ለውጦች የሚታይበት እድሜ ነው።

• ልጅ መውለድ – በእርግዝና ወይም ከወሊድ በሗላ በሚለዋወጡ ተፈጥሯዊ ኬሚካሎች ምክንያት እንዲሁም ልጅ ከወለዱ በሗላ በሚመጣው የሀላፊነት ስሜት ምክንያት ድብርት ሊያጋጥም ይችላል።

የድብረት ህመምን እንዴት መከላከል ይቻላል

• መደበኛ የሰውነት እንቅስቃሴ በማድረግ ንቁ ለመሆን ይሞክሩ

• ከቤተሰብ / ጓደኞች ጋር ይገናኙ – መገለል ድብርትን ያባብሳል። ጊዜ ይፍጠሩ እና ከሚወዷቸው ሰዎች ጋር ይገናኙ በአካል ካልተቻለ በስልክ ያግኙ። ከጓደኞችዎ ወይም ከቤተሰብዎ ጋር ጠንካራ ትስስር ይፍጠሩ።

• የትርፍ ጊዜ ማሳለፊያ ይምረጡ – በጣም የሚወዱትን እና ስሜትዎን ሊያሻሽል የሚችል ነገር ለማድረግ ይጣሩ ለአብነት፦በተፈጥሮ ውስጥ የተወሰነ ጊዜ ያሳልፉ ፣ በጎ ፈቃድ ስራዎች ይስሩ ፣ ይደሰቱበት የነበሩትን የትርፍ ጊዜ ማሳለፊያ (ወይም አዲስ መዝናኛ) መርጠው በመተግበር ጭንቀትዎን ይቀንሱ። ከሚያምኑት ሰው ጋር በመሆን በመልመጃዎች ወይም በትርፍ ጊዜ ማሳለፊያዎችዎ በመሳተፍ እና ደስ ሊያሰኝዎት በሚችሉ ሌሎች እንቅስቃሴዎች በመሳተፍ ጭንቀትን መቀነስ ይችላሉ ፡፡

• በቂ እንቅልፍ ለማግኘት ይሞክሩ – እንቅልፍ እና ስሜት በቅርብ የሚዛመዱ እንደመሆናቸው ጥሩ እና በቂ እንቅልፍ ለማግኘት ይሞክሩ፡፡ በአልጋ ወይም ሌላው ቀርቶ በመኝታ ክፍልዎ ውስጥ ሥራ መሥራት ከመዝናናት ይልቅ አልጋዎን ከጭንቀት ጋር እንዲያዛምዱት ሊያደርግ ስለሚችል ለመተኛት ብቻ አልጋዎን ይጠቀሙ።

• በጣም ወሳኝ የሆኑ የህይወት ውሳኔዎችን እስኪሻልዎት ያራዝሙ

• ከባድ ስራዎችን ወደ ትናንሽና መስራት ወደሚችሉት መጠን ይከፋፍሉ ፣ ቅድሚያ መሰጠት ያለባቸው ስራዎች ይለዩ እና የሚችሉት ያክል ብቻ ይስሩ

• እራስዎን በእራስዎት በመጠጥ ወይም በባለሙያ ባልታዘዘ መድኃኒት ለማከም አይሞክሩ።

ምንጭ የጤና ወግ

Leave a Reply